ታጣቂዎች በምዕራብ ወለጋ 10 ባንኮች ዘርፈዋል ተባለ


በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን 10 ባንኮች በታጣቂዎች መዘረፋቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ለDW ተናገሩ። ታጣቂዎቹ በዞኑ የአራት ወረዳዎች የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ማቃጠላቸውን እና  በሌሎቹ ወረዳዎች ዝርፊያ መፈጸማቸውን ገልጸዋል። አውዲዮውን ያዳምጡ።

የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገመቺስ ተመስገን ለDW እንደተናገሩት በመንግስት እና የግል ባንኮች ላይ ዝርፊያው የተፈጸመው ትላንት 10 ሰዓት ገደማ ነው። አስተዳዳሪው የታጠቁ ባሏቸው ኃይሎች ተፈጸመ ያሉት ዝርፊያ የተከናወነው በተመሳሳይ ሰዓት መሆኑንም ገልጸዋል።  

“የታጠቀው ኃይል እዚህ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እና በደረሰን መረጃ መሰረት 10 የሚሆኑ የመንግስት እና የግል ባንኮች ተዘርፈዋል” ብለዋል የዞኑ አስተዳዳሪ። ከተዘረፉት ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ሕብረት ባንክ እንዲሁም የኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ባንክ እንደሚገኙበት አስረድተዋል። በባንኮቹ ዝርፊያ የተወሰደው ገንዘብ መጠኑ ግን እስካሁን አለመታወቁን ጨምረው ገልጸዋል።  

የታጠቁት ኃይሎች በባንኮች ላይ ከፈጸሙት ዝርፊያ በተጨማሪ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን አቶ ተመስገን አክለዋል። በተለይ በዞኑ አራት ወረዳዎች ላይ ያሉ የመንግስት ተቋማት ታጣቂዎች አቃጥለው ሙሉ በሙሉ ማውደማቸውን አብራርተዋል። በዞኑ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው አራት ወረዳዎች ገንጂ፣ ባሎሳቢ፣ ዱግዶ እና አለታ ሲቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በምዕራብ ወለጋ ዞን የመከላከያ ሰራዊት ቢሰማራም የታጠቁት ኃይሎች በተመሳሳይ ሰዓት በየአካባቢው ጥቃት የሚያደርሱ በመሆናቸው ለመቆጣጠር ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል። 

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*