“ጫትን ማገድ ፈፅሞ የሚቻል አይደለም” ዶ/ር ዘሪሁን መሃመድ

BBC Amharic

ጫት ‘የኢኮኖሚ ዋልታ’ ተብሎ የተዘፈነለት ቡናን ከተካ ረዥም ጊዜያት ተቆጥረዋል። ገበሬዎች የቡና መሬታቸውን ወደ ጫት ማሳነት በመቀየር ጫትን የኑሮ ዋልታቸው ካደረጉ ቆይተዋል።በጥቅሉ በጫት የተሸፈነ መሬት ተስፋፍቷል ፤ የጫት ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል። ጫት እንደ ነውር ይታይ የነበረባቸው አካባቢዎች ቀዳሚ ጫት አምራችና ወደ ውጭ ላኪ እየሆኑም መጥተዋል።

Image result for ጫት

በቅርቡ ጫት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ቡናን መተካት ብቻም ሳይሆን ከቡና ይገኝ የነበረውን ገቢ በእጥፍ ማስገኘቱም ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ጫት አምራቾች እንዳሉም መረጃዎች ያሳያሉ።

በተቃራኒው ግን ጫት ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር እያስከተለ ያለው ማህበራዊ ቀውስም የአገሪቱ እራስ ምታት ሆኗል። በዚህ ምክንያትም በቅርቡ የአማራ ክልል ጫትን ማገድ የሚያስችለውን ረቂቅ አዋጅ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በክልሉ ገበሬዎች ጫትን ከማሳቸው መንቀል መጀመራቸውም እየተነገረ ነው።

• ጫትን መቆጣጠር ወይስ ማገድ?

በማምረት፣ በመጓጓዝ፣በማከፋፈልና በመሸጥ የበርካቶች ኑሮ የተመሰረተው ጫት ላይ መሆኑ በአንድ በኩል፤ የጫት ሱስ እያስከተለ ያለው ማህበራዊ ቀውስ በሌላ በኩል ጫትን ማገድ የሚለውን ጉዳይ ለብዙዎች አከራካሪ አድርጎታል።

ጫት ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት እንዲሁም በጫት ላይ በተካሄዱ አገራዊ የውይይት መድረኮች ላይ ጥናቶቻቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ዘሪሁን መሃመድን አነጋግረናል።

ዶ/ር ዘሪሁን ጫት ላይ የተሰሩ በርካታ ጥናቶችን ለህትመት ባበቃው የፎረም ፎር ሶሻል ስተደስ(FSS) አጥኚ ናቸው።

ዶ/ር ዘሪሁን

ቢቢሲ፦ ጫትን በሚመለከት ምን አይነት እርምጃ ነው መወሰድ ያለበት?

ዶ/ር ዘሪሁን፡ በአሁኑ ወቅት ጫትን በሚመለከት ሁለት ፅንፍ የያዙ አቋሞች አሉ። ጫት እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ጉዳት በመመልከት ጫት ይታገድ የሚል አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ጫት ለብዙዎች እንጀራና የኑሮ መሰረት በመሆኑ መነካት የለበትም የሚል ሌላ ፅንፍ አለ። ስለዚህ መከተል የሚኖርብን በሁለቱ መሃከል ያለውን መንገድ ነው። ጫት የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ጉዳት በብዙ ጥናቶች የተረጋገጠ ሲሆን ለጉዳቱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መጠበቅ የመንግስትና የማህበረሰቡ ግዴታ ነው። በአንፃሩ ደግሞ ጫትን የሚያመርተው ክፍል ያለው አማራጭ ምንድን ነው? ጫት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያመጣ ያለ በመሆኑ የሚተካውስ በምንድን ነው? የሚሉትን ነገሮች በጥልቀት መመልከት ያስፈልጋል።

ቢቢሲ፦መሃከል ላይ ያለው መንገድ ምንድን ነው?

ዶ/ር ዘሪሁን፡ መሃከል ላይ ያለው ጫትን እንዲሁ መልቀቅ ወይም ማገድ ሳይሆን መቆጣጠር ነው። ምናልባት መቆጣጠር የሚለው በትክክል ካልገለፀው Regulate ማድረግ ማለት ነው። የምንቆጣጠረው በምን መንገድ ነው? አሁን ባለው ሁኔታ ሲታይ ጫትን ማገድ በተለያዩ ምክንያቶች ፈፅሞ የሚቻል አይደለም። በተለያዩ አገራት እንደ ካናቢስ ያሉን ማገድ ኮንትሮባንድን እንዳስከተለ ጫትን ማገድ ከዚህ የዘለለ ውጤት አያመጣም። ምን አይነት አማራጮችን አቅርበን ነው የምናግደው? ጫት በአንዳንድ ቦታዎች ለምእተ አመታት ከባህልና ከማንነት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ማገድ ፖለቲካዊ ተፅእኖ ሊኖረውም ይችላል።

ቁጥጥር ማድረግም ቀላል አይደም ሰዎች በቀላሉ ጫት እንዳያገኙ ከፍተኛ ቀረጥ መጣል የሚል ሃሳብ የሚሰነዝሩ አሉ። በተቃራኒው ደግሞ ለምን ?ትንባሆና አልኮል ላይ ምን ያህል ቀረጥ ነው የሚጣለው በማለት ጥያቄ የሚያነሱም አሉ። ዞሮ ዞሮ በአጥኚዎች ዘንድ ክርክሩ በአመዛኙ ቁጥጥር ማድረግ ወደ ሚለው መጥቷል። ቁጥጥሩ ፣ እንዴት ይመረት? እንዴት ይጓጓዝ? እንዴት ጥቅም ላይ ይዋል? በሚለው ላይ የሚያተኩር ነው።

ቢቢሲ፦ መንግት የጫት ፖሊሲ ስለሌለው ጫት ላይ አቋም የለውም?

ዶ/ር ዘሪሁን፡ በጫት ላይ ፖሊሲ አለመኖር ብቻ ሳይሆን በጫት ላይ ውይይት ከጀመርን ራሱ ብዙ ዓመት አልሆነም። ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ብሄራዊ የጫት ውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ቀዳሚው ተቋም ነው። ብዙ ውይይቶችም ተካሂደዋል ቢሆንም ግን ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ተጨማሪ ምርምሮችና ውይይቶች ያስፈልጋሉ። ጫትን በሚመለከት ባሉ ፅንፍ አቋሞች የጫት ፖሊሲ ማውጣት ቀላል እንደማይሆን ይሰማኛል። ፖሊሲው ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ የብዙ አያሌ ሰዎችን ህይወት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ጉዳይን የሚመለከት መሆኑም ጉዳዮን እጅግ ከባድ ያደርገዋል።

በፖሊሲ ማውጣት ሂደት ጫት እየተቃመ ያለው በምን አይነት አውድ እና ባህል ነው ?የሚለው መታየት የሚኖርበት ሲሆን በሁሉም ክልሎችና አካባቢዎች እኩል ተፈፃሚ የሚሆን ፖሊሲ እናውጣ ማለት ግን አስቻጋሪ የሚሆን ይመስለኛል። ጫት መጀመሪያ ተገኝቶባቸዋል የሚባሉና ለረዥም ጊዜ ሲቃምባቸው የኖሩ አካባቢዎች እና ጫት ማብቀል ከጀመሩ አስር ዓመታት ብቻ ያስቆጠሩ አካባቢዎች አንድ አይነት መመሪያ ሊከተሉ አይችሉም። ስለዚህ አንዱ አማራጭ ሊሆን የሚችለው ክልል አቀፍ አማራጮችን ማውጣት ነው። ይህም ቢሆን ራሱ ጫት ክልል ተሻጋሪ ነው።

ጫት ላይ ጥናት ሰራን የምንል ሰዎች ብቻ ሳንሆን እታች ድረስ ያሉ ሰዎች የሚሳተፉበት ሰፊ ውይይት ያስፈልጋል። ከታች ያሉ ሰዎች አመለካከት በጣም ጠቃሚ ነው። ያኔ ነው የነጠረ ሃሳብ ይዘን መውጣት የምንችለው።

ቢቢሲ፦ጫትን ለመቆጣጠር የሚሞከረው አቅርቦት ላይ በማተኮር ነው?

ዶ/ር ዘሪሁን፡ አዎ አብዛኞቹ እርምጃዎች አቅርቦት ተኮር ናቸው። የዚህ አይነቱ እርምጃ ደግሞ ብዙ አያስኬድም። ዋናው ፍላጎት ላይ መስራት ነው።አሁን ያለውን ከፍተኛ የጫት ገበያ የፈጠረው ፍላጎት ነው። ይህ ፍላጎት ባይኖር ኖሮ ገበሬው ጫት ለማምረት ነጋዴውም ለማቅረብ አይበረታታም ነበር።

መቆጣጠሩ እንዳለ ሆኖ መጣር ያለብን ጫት ወደ መቃም የሚገባውን ሰው ቁጥር ለመቀነስ ነው። ይህ ደግሞ ህፃናትን ከጫት በመጠበቅ ነው። የጫትን አደገኝነት በመንገርና በማሳመን ወደ ሱስ እንዳይገቡ ማድረግ ነው። ለምንድን ነው ጫት መቃም እንደዚህ የተስፋፋው? የሚለውም መታየት አለበት። በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ተያያዥ የሆኑ ነገሮች አሉ። ምን ያህል የአካል ብቃት ማዘውተሪያ ቦታዎችና ቤተ መፃህፍት አሉን?

ቢቢሲ፦ማን ነው ከጫት እየተጠቀመ ያለው?

ዶ/ር ዘሪሁን፦እዚህ ጋር ጥቅምስ ጉዳትስ የገንዘብ ብቻ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ መነሳት አለበት። የገንዘብን ብቻ ከተመለከትን በአሁኑ ወቅት አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ጫት አምራቾች እንዳሉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በጫት የተሸፈነው መሬትም ምን ያህል እንደሆነ የማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል። ይህ የጫት አምራቾች የኢኮኖሚ ጥቅም እያገኙ እንደሆነ ግልፅ ያደርጋል። ጫት በብዛት የሚመረትባቸው እንደ ሀረርጌ ፣ ጉራጌ አካባቢና ሲዳማና የተወሰኑ የጌዲኦ አካባቢዎች ሲታዩ ከፍተኛ የህዝብ ጥግግት ያለባቸውና ከፍተኛ የእርሻ መሬት እጥረት ያለባቸው ናቸው። ስለዚህ ጫት በአነስተኛ ቦታ ላይ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ የሚመረት በመሆኑ ገቢው ቤተሰብ ለማስተዳደር ያስችላል። በዚህ የአምራቹ ተጠቃሚነት ጥያቄ የለውም።

በሌላ በኩል ከጅምላ ሻጩ ጀምሮ እስከ ቸርቻሪው ድረስ ያለው ሰንሰለት ሲታይ አንድ ጥናት 18 የሚሆኑ ባለድርሻዎችን ይዘረዝራል። ጫት ቆራጭ፣ አደራጅ፣ አመላላሽ(ትራንስፖርት)፣ መጠቅለያ የእንሰት ቅጠል የሚያቀርቡና ሌሎችም።

ስለዚህ ስለ ጫት ሲወራ ጫትን ስላመረተውና ስለተጠቃሚው ብቻ አይደለም። ይልቁንም በመሃከል ሰፊ የንግድ ትስስር አለ።

ክልልና ፌደራል መንግስትም እየተጠቀሙ ነው። በክልሎች ትንንሽ ኬላዎች ላይ ከጫት የሚሰበሰበው ቀረጥ ለአካባቢ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል። እንግዲህ ይህ ከቀረጥ ብቻ የሚገኝ ጥቅም ነው።

ቢቢሲ፦ ገዥው ምን ይጠቀማል?

ዶ/ር ዘሪሁን፦ ለአንዳንድ ሰው መዝናኛ ነው።በአንዳንድ ማህበረሰብ ደግሞ ጫት በማህበራዊ ትስስር ትልቅ ዋጋ አለው። ስለዚህ ይህም ጥቅም ነው። ከሃይማኖት ጋርም የሚያያዝበት ሁኔታ አለ።

በተቃራኒው ጫትን አላግባብ የሚጠቀሙ በጣም ይጎዳሉ።ቤተሰብ ይፈርሳል ማህበረሰብና አገር ይጎዳል።በጫት የሚደርሰው የአእምሮ ጤና ጉዳትም ከፍተኛ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*